አርቲስቶች እንዴት ከመከላከያ ጎን ሊቆሙ ይችላሉ?

አርቲስቶች እንዴት ከመከላከያ ጎን ሊቆሙ ይችላሉ?

“አገር ላይ አደጋ የተደቀነው አንቀጽ 39 የፀደቀ ጊዜ ነው”
                   (አርቲስት ደበሽ ተመስገን)
           
       ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የጠ/ሚኒስትር ፅ/ቤት በወቅታዊ የሀገራችን ጉዳይ ላይ የኪነ-ጥበብና የሚዲያ ባለሙያዎች ምን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ በሚል የኪነ-ጥበብ የሚዲያ ባለሙያዎችን እና እንዲሁም አትሌቶችን ጋብዞ ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች መካከል የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጥቂቶቹን አነጋግራ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው አጠናቅራለች።
ለኔ ይህ ጦርነት  የተጀመረው ዛሬ አይደለም።  ጦርነቱ ተጀመረ ብዬ የማምነው በ1987 ዓ.ም ላይ አንቀጽ 39 የፀደቀ ጊዜ ነው፡፡ ይህ አንቀፅ ሲጸድቅ፣ ኢትዮጵያዊነት እየፈረሰ ልዩነቶች እየሠፉ፣ ጀርባ መሰጣጠት ተጀመረ፡፡ አሁን ላይ  እየሆነ ያለው የዚያ ውጤት ነው፡፡ ዋናው ሰንኮፍ የተተከለው አንቀፅ 39 ላይ በ1987 ዓ.ም ነው፡፡
ስለዚህ መስራት ያለብን እንደነዚህ ያሉ ነገሮች ላይ ነው፡፡ ጦርነቱ ነገ ከነገ  ወዲያ ሊያልቅ ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ እነዚህ አመለካከቶች ያበቃሉ ወይ የሚለው ነው ዋና? የኔ ጥያቄ  ነው። እዚህ አስከፊ ውጤት ላይ ያደረሰን መሰረቱ ያ ነው ብዬ አምናለሁ።
ከዚህ ቀደምም በጣም ብዙ አዘንን። አሁንም በየዕለቱ የምንሰማቸው ነገሮች እጅግ የሚያስለቅሱና የሚያሳዝኑ ናቸው። አሁን የተጀመረው ጦርነት በመከላከያ ሰራዊታችን ድል አድራጊነት ተጠናቆ ሰላም እናገኝ ይሆናል፡፡
ነገር ግን የተተከለው ነገርስ….. በዚህ ብቻ ያቆማል? ወደ ሌላስ አይተላለፍም? ይህ አስተሳሰብስ በዚህ ያቆማል? አየሽ ትውልዱ ከዚህ አስተሳሰብ የፀዳ  መሆን አለበት። እናም ዋናው ሰንኮፍ ብዬ የምለው……. በዋናነት እዛ አንቀፅ 39 ላይ የተተከለው ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትን እንዳናስብ ያደረገን የሁላችንንም ልብ የከፈለው ይሄው አንቀፅ ነው፡፡ እውነት ለመናገር አሁን፤ አገራችን ላይ እየደረሰ  ባለው ነገር ለማዘን ኢትዮጵያዊነት ብቻ አይደለም የሚያስፈልገው ሰው መሆን በቂ ነው፡፡
ከዚህ አንፃር ኪነ-ጥበቡ ያለው ፋይዳና ሊሰራው የሚችለው ነገር ምንድን ነው ከተባለ አሁን ባለው ሁኔታ በተናጠል የምታደርጊያቸው ነገሮች አይኖሩም።
የኪነ-ጥበብ ስራ የቡድን ስራ ነው። የህብረት ስራ ነው። እኔ አንድ ነገር አበክሬ መናገር የምፈልገው፣ የአንድ ወቅት እሳት የማጥፋ ሥራ እንዳይሆን ነው፡፡
ዘላቂ በሆነ  መልኩ የአብሮነት፣ አንድነትና የአገር ፍቅር ላይ መስራት ያስፈልጋል  ብዬ አምናለሁ። ኪነ-ጥበቡ ምን ሊሰራ ይችላል በሚለው ላይ ግን በዚህ ዙሪያ የተቋቋመ ኮሚቴ አለ። የኮሚቴው አባላት አስተባብረው መስራት  የምንችለውን እንደ የሙያችን እንሰራለን። ምን መደረግም እንዳለበትም ሰሞኑን እናውቃለን። በተረፈ አሁን አገር ላይ የሆነው ነገር ከባድ ነው ያሳዝናል፤ አምላክ ሰላሙን ያምጣልን። ዘላቂ ሥራ ግን ያስፈልጋል።                  የሚከሰት ችግር የማይሽር ጠባሳ መጣል የለበትም”
                         (አርቲስት ተስፋዬ ማሞ)


               የሰሞኑ ሁኔታ እጅግ በጣም ከፍተኛ ሀዘን ነው ያሳደረብኝ። በአንድ ሀገር ውስጥ አለመግባባቶች፣ ግጭቶችና አለመስማማቶች ይኖራሉ። ነገሮቹ እንደየአግባቡ በውይይት፣ በድርድር ይፈታሉ። ከዚያም አልፎም ግጭት ውስጥ ሊገባ ይችላል።
ነገር ግን ግጭቶቹ  የሚያደርሱት ጠባሳ የማይሽር መሆን የለበትም። የተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ አላፊ መሆን አለበት። የሚከሰተው ነገር የከረረ ስሜትን ለማርገብ የሚውል እንጂ ቋሚ ጠባሳ ጥሎ ማለፍ የለበትም።
እኔ ለምሳሌ የልጅነቴንና የወጣትነት ዘመኔን ኤርትራ አሳልፌያለሁ፣ ሲቪል ሆኜም ቢሆን ከወታደሮች ጋር ኖሬ ወታደር ምን እንደሆነ አውቃለሁ። ውጊያዎችን በቅርብም በርቀትም የማየት አድል አጋጥሞኛል። ሰሞኑን በኢትዮጵያ እያየሁት ያለሁት ግን ከእነዚህ ሁሉ በጣም የራቀ፣ ጥቂት መፅሐፍ እንዳነበበና የሌሎች አገራት ተሞክሮዎችን እንዳየ ሰውም ስመለከተው፣ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው የተከሰተው።
የእኛ አገር ህዝብ ሃይማኖተኛ፣ ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው…. ባህሉ የተሳሰረ ነው። አሁን የተፈጠረው በተለይም ከሰሜን ኢትዮጵያ ህዝብ ስነ-ልቦና አንፃር ፈፅሞ የማይገናኝ ነው የሆነው።
ወታደር መግደልና መሞት ነው ስራው። ወታደር ቢገድልና ቢሞት ብርቅ ነገር አይደለም። ነገር ግን እንደ ባዕድ (ባዕድም ላይ ለማድረግ ነገሩ ይቸግራል) የገደሉትን አስክሬን ከብቦ መጨፈር፣ በተለይ በተለይ እርቃኑን አስቀርቶ ልብስ አስወልቆ፣ ድንበር አሻግሮ መልቀቅ ምን አይነት መልዕክት ለማን ማስተላለፍ እንደተፈለገ አይገባኝም። ይህ ድርጊት በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ የንቀት፣ ክብርን የማዋረድና ዝቅ የማድረግ ብሎም የኢ-ሰብአዊነት ድርጊት ነው። የኔ ሙያ ሰብአዊነትን ነው የሚሰብከው፤ ሌላ ስራ የለውም።
ኪነ-ጥበብ ሰዎች ውስጥ ሰብአዊነት እንዲያቆጠቁጥ ነው የሚሰራው፤ ሆኖም አሁን እንደ አገር የኪነ-ጥበብ፣ የባህል፣ የሃይማኖት ውድቀት ነው የገጠመን። ሁለንተናዊ ውድቀት ውስጥ ነው ያለነው። ሰው ተዘቅዝቆ ሲሰቀል ዝም አልን፤ አላረምንም።ስለዚህ ከመሰረቱ የተበላሸ ነገር አለን ማለት ነው። በሁሉም ነገር ውድቀት ውስጥ ገብተናል ማለት ነው።
ይህ ሁሉ ስር የሰደደ ነገር እንዲመጣና አሁን እያየን ያለነው ነገር እንዲከሰት ማን ነው በአግባቡ የቤት ስራውን ያልሰራው? ለተባለው ባለፈው ሳምንት አርብ አዳማ አንድ ስብሰባ ላይ  ተካፍዬ ነበር።  የከፍተኛ ትምህርትና አግባብነት ኤጀንሲ ያዘጋጀው ስብሰባ ነው። እዛ ስብሰባ ላይ ሙሉ ቀን ውዬ አንድ ነገር ተምሬ ተመለስኩ። የኤጄንሲው ዳይሬክተር አንዷለም አድማሴ(ዶ/ር) ንግግር ሲያደርጉ፤ “ዛሬ በሀገራችን የተፈጠረው ሁኔታ 20 ዓመት ቆጥሮ ውጤቱን ያየነው በትምህርት ስርዓታችን ላይ የተፈጠረ መጓደል ነው።” ብለዋል። አንድ የስርዓተ ትምህርት ውጤት በትውልዱ ላይ ተፅዕኖው  የሚታየው በአንድ ወይም በሁለት ዓመት አይደለም፣ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ይፈልጋል፤ በትንሹ 27 ዓመት ማለት ነው። ስለዚህ አሁን የምናየው ነገር የትምህርት ስርዓታችንና የግብረ ገብነታችን ውድመት ነው።
እኔ በውስጤ ፈሪሃ እግዚአብሔር አለ፤ ቲዎሎጂ ተምሬ ግን አይደለም፤ በስነ-ምግባር ውስጥ የማለፍ እድል የሚሰጥ  የአብነት ትምህርት ተምሬ ነው ያለፍኩት። አሁን አንደኛና ዋነኛ የውድቀቱ  ተጠያቂ የትምህርት ስርዓታችን ነው። የትምህርት ውድቀት ተያያዥ ነው። ለምሳሌ ጥበቡ በትምህርት የሚዳብር ነው። እነዚህ ሁሉ ተያያዥነት አላቸው። ዋናው ትምህርት  ከወደቀ ሁሉም ይወድቃሉ።
ሁለተኛው ሃይማኖት ነው። የሃይማኖት አባቶች ምንድን ነው የሚያስተምሩት?  የሁሉም ሃይማኖቶች አስኳል የሆነው ህግ “በራስህ እንዲሆን የማትፈልገውን በሌላው ላይ አታድርግ” አይደለም የሚለው? ይህ ጠፍቷል።
ስለዚህ በድፍረት የምናገረው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሃይማኖቶች በሙሉ ወድቀዋል። በዚህ የሚቆጣ ካለ ምንም ማድረግ አልችልም። ለምን? አሁን በአገራችን  እየተፈጸመ ያለው ሃይማኖት አለኝ ከሚል ህዝብና አገር የሚጠበቅ አይደለም። ሶስተኛው ተጠያቂ መንግስት ነው።
መንግስታት በተደጋጋሚ ወድቀዋል። ሲመጡም የማትንገራገጭ (የፀናች ሀገር) መስርተው እንደማለፍ የእነሱን ዋስትና የሚያረጋግጥና የሚፈልጉን ርዕዮተ ዓለም በመትከል፣ እነሱ በሌሉ ጊዜ የማይሰራ አድርገው ይቀርጹታል። ይኸው  እንዳየነው ንፁሀን ዋጋ ይከፍሉበታል። ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት በተደረገው ስብሰባ፤ አሁን የምናየውንና የሚጨበጥ ችግር መከሰቱ ተነስቷል። ይህን ችግር እንዴት አድርገን እንፍታው? በሚለው ዙሪያም ተወያይተናል። እንግዲህ የሰው ልጆችን አዕምሮ የመስራት ጉልበት ያለው ኪነ-ጥበቡ፣ ዘላቂ ስራ ሊሰራበት የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡
ሁለተኛው አሁን ጦርነት አለ፣ ገዳይ አለ፣ ሟች አለ። ስለዚህ በዲፕሎማሲና በውሸት ፕሮፓጋንዳ የአገሪቱ ጠላቶች የበላይነት እንዳያገኙ መመከት ስለሚያስፈልግ፣ ለአገራችን ምን አይነት አስተዋፅኦ እናድርግ? በሌላ በኩል፤ የኪነ-ጥበቡ መንደር የረጋ ማህበረሰብ ለመፍጠር በዘላቂነት የሚሰራበት መዋቅር ተዘርግቶ እንዲቀጥል የሚል ውሳኔ ላይ ነው የተደረሰው።
ጠቅለል ሳደርግልሽ፤ አሁን ድንገት ችግር ተፈጥሯል፣ ለድንገተኛው ነገር ችግሮችና ወደፊት  ምን መሰራት አለበት በሚል ነው ምክክሩ። እኔ በግሌም ሆነ ከሙያ አጋሮቼም ጋር የሚፈለግብኝን ለመስራት በዝግጅት  ላይ ነኝ።  


                “ጦርነቱ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይጀመራል ብዬ አምናለሁ”
                         (ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ)


            አሁን ላይ ለኢትዮጵያ የተሻለ ጊዜ ሊመጣ ነው የሚል ስሜት ነው ያለኝ። በኢትዮጵያ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብዬ ነው የማስበው። አሁን ያሉ ሁኔታዎችን ስንመለከት፤ ከዚህ በኋላ ህውሃት የሚባል ፓርቲ አይኖርም። በሌላ በኩል ክልሉን ነፃ የማውጣቱም ነገር ቢሆን ቀናት የሚፈጅ እንጂ ብዙ የሚረዝም አይመስለኝም። ረጅም ጊዜም ቢወሰስድ እንኳን ባለ ድል የሚሆነው የፌደራል መንግስት ነው ብዬ አምናለሁ ። ለምን? ቢባል መንግስት የመላ ሃገሪቱን የትግራይንም ህዝብ ጭምር ስለያዘ አሸናፊነቱ አያጠራጥርም።
በአጠቃላይ ጦርነቱ ብዙ ብዥታዎችን የሚያጠራ ነው ብዬም አምናለሁ። ለምሳሌ አንዱ ብዥታ፤ “የትግራይ ህዝብ ከህወኃት ጎን ነው” የሚል ነበር። በሂደት እንዳየሁት፣ የትግራይ ህዝብ ከህወኃት ጎን አይደለም። እንዴት ይህን አልክ ከተባልኩ  አሁን መንግስት እየተቆጣጠረ ነፃ ባደረጋቸው ቦታዎች ላይ የትግራይ ህዝብ ከህወሃት ጎን ቢሆን ኖሮ፣ ምንም እንኳን መንግስት በሃይል ቢያሸንፍ እንኳን ከብዙ ህዝብ እልቂት በኋላ ይሆን ነበር። ግን እስካሁን የህውኃት መሪዎችም በሚጠቀሟቸው የመገናኛ መስኮቶች “ይህን ያህል ህዝብ መንግስት ጨረሰብን” ሲሉ አልሰማንም።
መንግስት በተቻለ መጠን ንፁሀን እንዳይጎዱ ጥንቃቄ አድርጓል። መንግስት የሆኑ ሰዎችን ለመያዝ ከስር ያሉትን እያጠፋ የመሄድ ፍላጎትም የለውም፤ አግባብም አይደለም። እስካሁን በንፁሃን የትግራይ ህዝብ ላይ ደረሰ የተባለ ጉዳት አልሰማንም፡፡ ህወሃትም አልነገረንም። መንግስት በስህተትም ቢሆን ንፁሃንን ቢነካ ይጮሁ ነበር።
በአጠቃላይ ይሄ የተፈጠረው ጦርነት ሲጠቃለል፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ትልቅ መሰረት ይጥላል ብዬ አምናለሁ። የብዙ አካላት አቅም ታይቷል። በሌላ በኩል አገሪቱ ላይ በተለያየ አቅጣጫ የተነሱ የሽብር መስመሮች ሁሉ ወደ መርገብና ከዚያም ወደ መጥፋት ይሄዳሉ።  ይህ የሚሆነው ግን ህወሃት ሲጠፋ ማንም ስለማይደግፋቸው አይደለም (እርግጥ አሁንም ህውሃት ከጀርባቸው አለ)። የህዝቡን አቅም እነሱም አይተውታል። ቀደም ሲል ህዝቡ ለጠቅላይ ሚንስትሩም ለብልጽግና ፓርቲም አሉታዊ ስሜት ነበረው። ነገር ግን እነዚህ ስሜቶች ያሉባቸው አካባቢዎች በሙሉ በአገር ጉዳይ ሲመጡባቸው፣ህዝብ በከፍተኛ ሁኔታ ከመንግስት ጎን ቆሟል። ጉዳዩ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ግንኙነት ስለሌለውና የአገር ጉዳይ ስለሆነ ብቻ ማለት ነው። በተግባር ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ብልፅግናን ሲቃወሙ የነበሩ ሰዎች እንኳን የአገርን አንድነት ለድርድር ሳያቀርቡ ለአገራቸው ከመንግስት ጎን ቆመው እያየን ነው።
ሌላው ይሄ ጦርነት ከብዥታ ያጠራልንና የገለፀልን ነገር  ህወሃቶችም ሆኑ ሌሎች ሃይሎች መከላከያ ሰራዊቱ የተከፋፈለ ነው ይሉ ነበር። “አገሪቱ የተከፋፈለች ናት።” አያድርገው እንጂ አንድ ነገር ቢመጣ እንፈርሳለን” ይባል ነበር። ይሄ አስተሳሰብና ስጋት መሰረታዊ ስህተት ያለበት መሆኑን አይተናል ።  በዚህ ጦርነት  መከላከያ ሰራዊት እጅግ የተከበረ ሀይል መሆኑን ነው ያነው። ሰው ሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰውንና አንዳንድ የሰራዊቱ አካላት ከህወሃት ጋር መሆናቸውን ሲያይ ስጋት ሊይዘው ይችላል።  ነገር ግን የሰራዊቱን አንድነት፣ ጀግንነትና አገር ወዳደድነት እንዲሁም የትግራይ ህዝብ ከህወሃት ጎን አለመቆሙን ያየንበት ነው። አሁንም በሰራዊቱ ውስጥ ብዙ የትግራይ ተወላጆች አሉ በጡረታ ተገልለው ወደ መሪነት ከተመለሱት ጀነራሎች አንዱ የትግራይ ተወላጅ ናቸው። አሁን እየሆነ ያለው ሁላችንም እንደሰጋነው አይደለም። ይሄንን የምለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ብልፅግና ስለነገረኝ አይደለም። እውነታ ነው።
እንግዲህ የተከሰተው ጦርነት ለኢትዮጵያ አይገባትም ነበር፤ በተለይም 60 ሺህ ገደማ ልጆቹን ገብሮ የ1983ቱን ለውጥ ላመጣው የትግራይ ህዝብም አይገባውም። ከዚያ በኋላ ጥቂቶች ባለሃብት ሆኑ ልጆቻቸው በውጭ በድሎት እየኖሩ ነው።  አሁን በትግራይ ጦርነት ሲነሳ የእነሱ ልጆች ወላፈኑ አይነካቸውም። አሁንም የድሃ የትግራይ ልጆችን ወደ እሳት ለመጨመር የተደረገው ነገር ያሳዝናል። በዚህ ጦርነት የትግራይን ህዝብ ጨዋነት አይተንበታል። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትም በጣም የሚደንቅ ነው። ከአሁን በኋላ ህውሃት ቢጠፋ እንኳን ኦነግ በይው ኦነግ ሸኔ ወይም ሌላ ስም ስጪው…. አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ የሆነ ቦታ ጥፋት እያደረሰ መኖር እንደማይችል የታየበት ነው። ለምሳሌ የአማራ ተወላጆችም ብዙ ቦታ በጣም ብዙ ጥቃት ደርሶባቸዋል። የአማራ ህዝብ ግን ምን ያህል ታጋሽ እንደሆነ አሳይቷል። ህወሃት ላይ ለመዝመት ለምን በወረፋ አይደርሰንም እያለ እየሰማን ነው። ከዚህ ከአማራ ህዝብ ሌላው ብዙ ይማርበታል ብዬ አምናሁ።
ወደ አርቲስቶቹ የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ስብሰባ ስመለስ አንደትገልጪው የምፈልገው፤ መንግስት የፓርቲ አባላት፣ የወጣት አደረጃጀት፣ የሴቶች ሊግ የሚባሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉት፤ ነገር ግን ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ለሚዲያ አካላት ቅድሚያ ሰጥቶ ጦርነቱ በተነሳ በሳምንቱ ነው ጥሪ ያደረገው። ይህ ማለት መንግስት ሚዲያውና ኪነ-ጥበቡ ለውጥ ያመጣል ብሎ እንዳመነ በደንብ ያሳያል። ኪነ-ጥበብ ትልቅ ሀይል ያለው መሆኑን በደንብ አሳይቷል። ነገር ግን የኪነ-ጥበብ ማህበረሰብና ደራሲያን የሚባሉት ሰዎች እዛ መድረክ ላይ ሲያነሱ የነበረው ነገር እጅግ የሚያሳፍር ነበር።
መንግስት “ እሳት ተነስቷል ኑ፣ ይህን እሳት እንዴት በጋራ እንደምናጠፋው እንምክር” እያለ የኪነ-ጥበብ ባለሙያው፣ስለ ህገ-መንግስት መሻሻል፣ የብሔር ነገር ከእዚህ አገር ካልጠፋ የሚሉ ነገሮች ነበር የሚያወሩት፡፡ አሁን የድንገተኛ ነገር ነው የተጠራንበት። መንግስት ጦርነቱን ሲጨርስኮ ዝም ብሎ አይቀመጥም። ብዙ ስራዎች አሉት። መንግስትም ህዝብም በቀጣይ አገራችን እንዲህ አይነት ችግር ውስጥ  ዳግም እንዳትገባ ምን ማድረግ አለብን? ምን ይሰራ የሚል ሃሳብ ማንሳቱ አይቀርም  እኮ። እርግጠኛ ነኝ ህወሃት የተከተለው ነገር ነው ለዚህ ሁሉ ያበቃን፣ ...እንዴት እንላቀቀው ብሎ ህዝቡ በተለያየ መንገድ መጠየቁ አይቀርም። መንግስትም የተረዳው ነገር አለ፡፡ ያኔ አሁን አርቲስቶቹ የሚሏቸውን ነገሮች ይናገራሉ። በስብሰባው እኮ “የአሁን አንበጣና የዱሮ አንበጣ ልዩነት አለው። የድሮው ይበር ነበር፤ የአሁኑ ግን ጣሪያ ላይ ያርፋል” እኮ ነበር የሚሉት። አንቀፅ 39 የሚሉም ነበሩ። ስለዚህ የነበሩት የኪነ-ጥበብ ሰዎች በተፈለጉበትና በተሰጣቸው ቦታ ላይ አልነበሩም። እኔ በጣም ነው የማዝነው። ያኔ የህወሃት 40ኛ ዓመት ሲከበር ሄደን ነበር። መቀሌ ደደቢትና ሌሎች ቦታዎችን ጎብኝተናል። እዛ ቦታ ላይ ህወሃትን “በአፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ ልዩ ሀይል ነው፤ ታሪኩ በመፅሀፍ ካልታጸፈ በፊልም ካልተሰራ ደደቢት ሚዚየም ካልሆነ….” ሲሉ የነበሩ ሰዎች ያንን ረስተው አሁን እንዴት ግዳጃቸውን መወጣት እንዳለባቸው ሲደነፉ በጣም ነው ያፈርኩት።
በነገራችን ላይ እነማን ምን ነበሩ፣ እነማን ከህወሃት ጋር ነበሩ፣ ምን ጥቅም  ነበራቸው የሚለው ወሬ ሳይሆን ሪከርድ የተደረገ በግለሰቦችም በድርጅቶችም  የሚገኝ ማስረጃ ነው።
ግዴለም ያኔም ከህወሃት ጎን ይሁኑ የፈለጉትን ይናገሩ፤ ህዝብ ይቅርታ ሳይጠይቁ ምንም ሳይናገሩ ያገኙትን ማሊያ እየለበሱ መንከረባበት ግን ደስ አይልም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እኮ ከህወሃት ጋር ሰርተዋል። የሰራዊቱም አባል ነበሩ። እሳቸው በአደባባይ በግልፅ ህዝብን በተደጋጋሚ ቅርታ ጠይቀዋል። አንቺ ጠንቋይ ቤት ስትመላለሺ ከርመሽ ወደ እግዚአብሔር የምትመለሽው እኮ ሹልክ ብለሽ አይደለም። ንስሀ ገብተሸ “ይቅር  በለኝ፤ የእስከዛሬው መንገዴ ስህተት ነው” ብለሽ እንጂ ዝም ብለሽ አይደለም። እንደዛ ከሆነም ተቀባይነት የለሽም። እኔ 40ኛ አመቱ ላይ መቀሌ ሄጃለሁ። የብሄር ብሄረሰቦችም ጊዜ ጅጅጋ ሄጃለሁ፡፡ አንድም ቀን ከህወሃት ጎን አልነበርኩም፤ ወደ ህዝብ ወደ ሌላ ባህልና አካባቢ ስሄድ ደስ እያለኝ ነው የምሄደው። ነገም ብልፅግና እንዲህ አይነት ጉዞ ቢያዘጋጅ እሄዳለሁ። የምሄደው ወደ ሌላው አካባቢ የአገሬ ህዝብና መሬት ነው፡፡ ከብልፅግና ጎን ግን አልቆምም፡፡ ዞሮ ዞሮ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቹ አሳፍረውኛል። ከኪነ-ጥበብ ይሄ አይጠበቅም።
መጨረሻ ላይ በስብሰባው ሲወሰን፤ የኪነ-ጥበብ ማህበራቱ “ይህን ይህን ቢያደርጉ ነው” የተባለው፡፡ እኔ እንድታሰፍሪልኝ የምፈልገው እርግጠኛ ነኝ….. እነዚህ ማህበራት አሁን ለተፈጠረው ችግር አንዳችም ለውጥ ሳያመጡ ጦርነቱ ይጠናቀቃል። ህዝቡን አነቃቅተው ከአገሩና ከወገኑ ጎን እንዲቆም የማድረግ ስራ ይሰራሉ ብዬ አላምንም። አይሰሩም።