ከበደች ተክለአብ አርአያ

ከበደች ተክለአብ አርአያ

ሰዓሊ፣ ቀራጺ፣ ገጣሚ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህርት

     የሥነ-ጥበብ ትምህርት መማር የጀመርኩት በአዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ ሥነ-ጥበብን የመሥራት ፍላጎት እንጂ በሥነ-ጥበብ ሙያ እተዳደራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ሕይወት ግን መንገዴን ወደ ሥነ-ጥበብ አቅጣጫ መራችው:: በደርግ የአገዛዝ ዘመን በተካሄደው የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳትፎ በማድረጌ መታደን ስጀምር፣ በጅቡቲ በኩል ለማምለጥ ሞከርኩ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በወቅቱ ሶማሊያና ኢትዮጵያ በድንበር ግጭት ውስጥ ስለነበሩ፣ ድንበር ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች በቁጥጥር ሥር አዋሉኝ፡፡ ቀጣዮቹን አስር ዓመታት ያሳለፍኩት በሶማሊያ እስር ቤቶችና በጉልበት ሥራ ካምፖች ውስጥ ነበር፡፡ ሕይወት ግን ለሁሉም ነገር ምክንያት ነበራት፡፡ ሚልቪን ራዳር ‹በገሃዱ ዓለም የምናስተናግዳቸው ሽንፈቶቻችን፣ በሥነ-ጥበቡ ዓለም ድሎቻችን ይሆናሉ፡፡ በሥነ-ውበት ዓይን ሲታይ፤ በችግሮቻችን፣ በስቃዮቻችንና በሽንፈቶቻችን ከመማረር ይልቅ ወደ ሥነ- ጥበብ ሥራነት በመቀየር፣ እንዲሁም በመውደድ የኋላ ኋላ በቁጥጥራችን ሥር እናደርጋቸዋለን›› በማለት ጽፋለች፡። በእስር ቤት ያሳለፍኳቸው ዓመታት፣ ከተቀረው ዓለም የሰው ልጅ ጋር ትስስር ለመፍጠር ሰበብ ሆነውኛል፡፡ ለሥነ-ጥበብ ሥራዎቼ የመነቃቃት ምንጭ የሆኑኝም እነዚያ የግዞት ዓመታት ናቸው፡፡
የተወለድኩት በ1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ መርካቶ በሚባለው ሰፈር ነበር፡፡ መጠነኛ ገቢ ያላቸው ወላጆቼ፣ ካፈሯቸው አራት ልጆች፣ እኔ የመጨረሻዋ ነኝ፡፡ ዛሬም ድረስ ታላቅ አርአያዬ፣ አሁን በሕይወት የሌለችው እናቴ ናት፡፡ እናቴ፣ መንፈሳዊውን ዓለም ከምድራዊው ዓለም ጋር በሚገርም ሁኔታ አጣጥማ ሕይወቷን ስትመራ የኖረች፣ ፍጹም ሃይማኖተኛ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበረች፡፡ መደበኛ ትምህርት ባትከታተልም፣ እጅግ ብሩህ አእምሮ ያላትና ለሥነ ጽሑፍ ፍቅር የነበራት ሴት ናት፡፡ የማክሲም ጎርኪን መጽሐፍት አነብላት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከጎርኪ ሥራዎች፣ ‹እናት› ለሚለው ረጅም ልቦለድ የተለየ አድናቆት ነበራት፡፡ አማርኛ ማንበብና መጻፍ የቻለችው በራሷ ጥረት ነበር:: ለሥነ ግጥም፣ በተለይ ደግሞ ለቅኔ እንዲሁም ለቲያትር የተለየ ፍቅርና የፈጠራ ተሰጥኦ የተቸራት እናቴ፤ የራሷን የጥልፍ ዲዛይኖች ትፈጥርም ነበር፡፡ ለፍትህ መከበር ጠንካራ አመለካከት የነበራት ሲሆን ከቁሳዊ ስኬት ይልቅ ለእሴቶች ደንታ ከነበራቸው ጥቂት ሰዎች አንዷ ነበረች፡፡ በትምህርት አስፈላጊነት ላይ ጥብቅ እምነትም ነበራት፡፡ አባቴ ወደ መቀሌ ከተማ ሄዶ መድሃኒት ቤት ሲከፍትና ፊቱን ወደ ንግድ ሲያዞር፣ እሷ ግን እኛን ልጆቿን ለማስተማር አዲስ አበባ መቅረትን መረጠች፡፡ ከትምህርት ቤት ስንመለስ፣ ውሏችንንና የተማርነውን ትጠይቀንና የቤት ሥራችንን በአግባቡ እንድንሰራም ታበረታታን ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ የእንግሊዝኛ መምህራን፣ መጻሕፍትን ሲያነቡልን በጽሞና አዳምጣቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይሄን የማደርገው፣ ወደ ቤቴ ስመለስ ታሪኩን በአግባቡ ለእናቴ ለመተረክ ስል ነበር፡፡ እናቴ ሁሌም ከጎኔ ነበረችና በተደጋጋሚ ባጋጠሙኝ ፈታኝ የመከራ ጊዜያት ሁሉ በጽናት እንድቆም ደግፋኛለች፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ፣ ሥነ ጽሑፍ የመማር ሃሳብ ነበረኝ፡፡ ንባብ ነፍሴ ነበር፤ ግጥም ስወድ ደግሞ ለጉድ ነው፡፡ ቅኔ የመማር ከፍተኛ ፍላጎትም ነበረኝ፡፡ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እየሄድኩ ግዕዝ መማር የጀመርኩትም፣ ገና በልጅነቴ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ በየጉራንጉሩ ግጥሞችን እየጻፉ መበተን ትልቅ የትግል ስልት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ግጥሞችን መጻፍ የጀመርኩት፡፡ በእርግጥ የስዕል ስሜትም ነበረኝ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሆኜ፣ የሳይንስ ትምህርት ስዕሎችን መሳል እወድ ነበር፡፡ በስተመጨረሻም ስዕልና ቀለም ቅብ ይወዱ የነበሩት ወንድሜና አንድ ጓደኛዬ ባሳደሩብኝ ተጽዕኖ፣ አሥራ አንደኛ ክፍልን እንደጨረስኩ፣ ሥነ-ጥበብ ለማጥናት ወስኜ፣ በ1968 ዓ.ም አዲስ አበባ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅም ትምህርቴን ተከታተልኩ፡፡
በቀበሌና በወጣት ሊግ አማካይነት በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጠልኩበት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ወታደራዊው መንግሥት የቀይ ሽብር ዘመቻን አውጆ፣ ተማሪዎችን ከያሉበት እያደነ፣ ማሰርና በጅምላ መጨፍጨፍ ሲጀምር፣ እኔም ለዚህ ክፉ ዕጣ ከታጩት ታዳኝ ተማሪዎች አንዷ መሆኔን አወቅሁት፡፡ ከተጋረጠብኝ አደጋ ማምለጥ ነበረብኝና ለአንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ከሌሎች አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀን ቆየን፡፡ በስተመጨረሻም ድንበር አቋርጠን ጅቡቲ ለመግባትና ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ፣ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወጣን:: በድብቅ ድንበሩን ሊያሻግሩን ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎች ብናገኝም፣ ሙከራችን ግን እጅግ አደገኛ ነበር፡፡ አቋርጠነው ልናልፍ ባሰብነው ድንበር ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ገጥመው ኖሮ፤ ይሄንን ሳናውቅ በእግራችን በመጓዝ የሶማሌ መደበኛ ጦርና የሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች ሰፍረውበት ወደነበረው የጦር ካምፕ ሰተት ብለን ገባን፡፡ ወዲያው በቁጥጥር ስር ውለን ወደ ሶማሊያ ተወስደን ታሰርን፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከሦስት ዓመታት ጦርነት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ እኛ ግን ቀጣዮቹን አስር ዓመታት በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ሥራ ካምፖች ውስጥ አሳለፍነው፡፡ በስተመጨረሻም በኢጋድ ስብሰባ ላይ በተደረገ ስምምነትና በዓለማቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት አግባቢነት፣ ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኞች ሆኑ፡፡ እኛም በ1981 ዓ.ም ከእስር ተፈታን፡፡
እነዚያ በእስር ያሳለፍናቸው ዓመታት እጅግ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ከእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውጪ ካለው ዓለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረንም፡፡ ከጉሮሮ የማይወርድ ምግብ እየበላን፣ ንጽህና በጎደለው ማጎሪያ ውስጥ አስከፊ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ውለን ማደር ነበረብን፡፡ ወባና በደም መበከል የሚፈጠር በሽታ፣ ዘወትር ከእስር ቤቱ የማይጠፉ የተለመዱ የእስረኞች የስቃይ ምንጮች ሲሆኑ ከወህኒ ልንፈታ አንድ አመት ሲቀረን ደግሞ በኮሌራ ወረርሽኝ ተጠቅተናል፡፡
እስር ቤት ውስጥ፣ ፍጹም ስለ ራሳቸው ግድ የሌላቸው አልያም ፍጹም አደገኛና ራስ ወዳድ ሰዎችን ልታገኙ ትችላላችሁ፡፡ እናም ከእኛ ጋር ሁሉም አይነት ሰዎች ነበሩ፡፡ ፈጣሪ ከዚያ መከራ ያተረፈኝ ለእናቴ ብሎ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እሷ ለኔ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ ትልቋ ስጦታ ነበረች:: እንደ እስረኛ በቁሳቁስ ሳይሆን መከራን አብሮ በመጋፈጥ እርስ በርስ እንረዳዳ ነበር፡፡ የጽሁፍ መሳሪያዎች በማገኝበት አጋጣሚ ሁሉ፣ የመድሃኒት ፓኮዎችንና የዱቄት ወተት ክርታሶችን እንደ ወረቀት እየተጠቀምን በርካታ ግጥሞችን ጽፌያለሁ:: እርግጥ በአማርኛ መጻፍ ክልክል ስለነበር፣ የጻፍኳቸውን ግጥሞች በየስርቻው እደብቅ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ግጥሞቼ በአይጥና በድመት ተበልተዋል፣ በርካቶችም ጠፍተዋል፡፡ ያኔ መጻፍ መቻሌ ከአዕምሮ መቃወስ አድኖኛል፡፡ ቀስ በቀስ ትምህርት ቤት አቋቁመን ፊደላትን በማስቆጠር እስረኞችን ማስተማር ጀመርን፡፡ ሳይንስና እንግሊዝኛን የመሳሰሉ ትምህርቶችን አስተምር የነበረ ቢሆንም ትልቁ አስተዋጽኦዬ አማርኛ ማስተማሬ ነበር፡፡ የተለያዩ ታሪኮችና ግጥሞችን እየጻፍኩ ለማስተማሪያነት እጠቀምባቸውም ነበር፡፡ እኛ ከእስር ስንፈታ፣ እስረኛው ሁሉ ማንበብና መጻፍ ይችል ነበር፡፡ ትምህርቱም እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል አድጎም ነበር፡፡ መጽሐፍትን የምናገኘው አልፎ አልፎ ነው:: በተለየ ሁኔታ የማስታውሳቸው፣ የፕሪሞ ሌቪን መጽሐፍትና የአሌክስ ሄሊን ‹ሩትስ› የተሰኘ መጽሐፍ ነው፡፡ በሄሊ መጽሐፍ ውስጥ የተሳሉት የመስክ ሠራተኞች ሕይወት፣ ከእኛ ሕይወት ጋር በሚገርም ሁኔታ መመሳሰሉ ቀልቤን ማርኮት ነበር፡፡ ራሳችንን ዋጋ እንዳለው ሰብአዊ ፍጡር እንድናስብ ያገዙን እነዚህ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፡፡
ወንድሜ እኔን ፍለጋ አዲስ አበባ መምጣቱን ሰምቼ ስለነበር እንደተፈታሁ ወዲህ ወዲያ ሳልል በቀጥታ የመጣሁት ወደ አዲስ አበባ ነበር፡፡ በወቅቱ ወንድሜ ያንን ማድረጉ ለእኔም ሆነ ለእሱ አደገኛ ስለነበር ከስድስት ወራት በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቄ፣ መላው ቤተሰቦቼ ወደ ሚኖሩባት አሜሪካ አቀናሁ፡፡ ከረዥም ጊዜያት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከእናቴ፣ ከወንድሜ፣ ከእህቴና ከቀሩት ቤተሰቦቼ ጋር ለመቀላቀል ቻልኩ፡፡ ለዓመታት ያቋረጥኩትን የሥነ-ጥበብ ትምህርት በመቀጠልም፣ በዋሽንግተን ዲሲው ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በሥነ-ጥበብ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ፡፡ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ግሩም መምህራን ገጥመውኛል፡፡ ሁለት ድንቅ መካሪ ዘካሪም አግኝቻለሁ - የሥነ-ጥበብ መምህሬ እስክንድር ቦጎሲያንና የፊልም መምህሬ አብይ ፎርድን፡፡ ከእስክንድር ጋር በመሆን ኔክሰስ የተባለ ሥራ ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመሥራት እድል አግኝቻለሁ፡፡
በስዕሎቼ ስሜቶቼን፣ ትዝታዎቼን እንዲሁም ጊዜና ቦታ ከሚገድባቸው ግላዊ ገጠመኞቼ ዘመን እስከ ማይሽራቸው ዓለማቀፍ ጉዳዮች የተዘረጋውን ምናቤን መግለጽ ጀመርኩ፡፡ ራሴን በግላዊ ገጠመኞቼና ልምዶቼ ላይ ብቻ አልገደብኩም:: ምናቤን ሰፋ በማድረግ ጦርነት፣ ስቃይና በስተመጨረሻም ፈውስን ወደመሳሰሉ ዓለማቀፍ ጉዳዮች ውስጥ ገባሁ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ፣ በቀላሉ የሚለዩ ተረኮችን በመጠቀም የግል ልምዶቼን በአለም ዙሪያ ከሚታዩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር እያስተሳሰርኩ፣ ኤክስፕሬሽኒስት በተባለው የአሳሳል ዘዬ ስዕሎቼን እሰራ ነበር፡፡ በመቀጠልም እንደ ወትሮው ሁሉ ትኩረቴን በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ፣ ከቀድሞዎቹ በበለጠ ምስል አልባ የሆኑ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መሥራት ጀመርኩ፡፡ ከዚያም ቴክስቸር፣ ቀለምና ቅርጽን በመሳሰሉ የእይታ መሠረታዊ ነገሮች በመጠቀም፣ ስሜትን የሚያጭሩ፣ ሙሉ ለሙሉ ምስል አልባ ስዕሎችን መሳል ቀጠልኩ፡፡ አሁን ባለሁበት ሁኔታ፣ ብርን የመሳሰሉ ባህላዊ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በመገጣጠም እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ብር በውስጡ ብርሃን የሚያሳልፍ በመሆኑ እወደዋለሁ፡፡ ከሌሎች ቁሳቁሶች ጋር በመሸመን፣ የተለያዩ ተደራራቢ ትርጉም ያላቸው መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ ስዕሎችንና ቅርጾችን ከሥነ-ግጥም፣ ሙዚቃና ሥነጽሑፍ ጋር እያዋሃድኩ የራሴን ህብር እፈጥራለሁ፡፡ አንደኛው ጥበብ በሌላኛው እንዲሁም በእኔ ላይ መነሳሳትና ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡
ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ በስቱዲዮ ሥራዬን እየሰራሁ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሥነ-ጥበብ ትምህርት አስተምር ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጆርጂያ በሚገኘው ሳቫና የሥነ-ጥበብና የዲዛይን ኮሌጅ እያስተማርኩ እገኛለሁ፡፡ ማስተማር ያስደስተኛል፡፡ ምክንያቱም ራሴን ሙያው ከደረሰበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለማድረስ ስል በስፋት እንዳነብና ጥናት እንዳደርግ ያስገድደኛል፡፡ ሌላው ማስተማርን እንድወደው የሚያደርገኝ ደግሞ፣ የተማሪዎቹ ሥራዎች ብዙ ጊዜ ፈጽሞ ወደ ማላውቃቸው ሥነ-ጥበባዊ ጉዞዎች ይዘውኝ ስለሚሄዱ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ባስተምር ደስ ይለኛል፤ በሙያዬ የማበረክተው አስተዋጽኦ በእነዚህ አገራት የተሻለ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላልም ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ቀን የሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሰዓሊ የምሆንበትና በጽሁፍ ሥራ ላይ ብዙ ጊዜዬን ማሳለፍ የምችልበት ዕድል ይፈጠርልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሥነ-ጥበብ ለኔ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ሥነ-ጥበብን ሙያዬ ለማድረግ የቻልኩት አንድም ለቁሳዊ ስኬት ደንታ ስለሌለኝ፤ ሁለትም ሙያው የሚጠይቀው ዲስፕሊንና ሙሉ ትኩረት ስላለኝ ይመስለኛል፡፡
የዛሬ ዘመን ወጣት ሴቶት ትኩረት ሊሰጧቸው የሚገቡ ጥቂት ነገሮች አሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በመጀመሪያ አደጋዎችን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው፡፡ ፈቃደኛ ካልሆኑ ምንም ነገር ሊያሳኩ አይችሉም፡፡ አደጋን መጋፈጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰርፀው የኖሩ አመለካከቶችን መዳፈር ሊሆን ይችላል፡፡ ሴቶች ይህን ማድረጋቸው ህልማቸውን ለማሳካት ያግዛቸዋል፡፡
ሆኖም አደጋን መጋፈጥንና ከባህል ልንማራቸው የምንችላቸውን ነገሮች አመጣጥኖ ማስኬድም ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ወጣት ሴቶች እውቀት ለመቅሰም ይሻሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እውቀትን ፍለጋ ሲተጉ ደግሞ እጅግ ብዙ መልካም ነገሮች መከተላቸው አይቀርም፡፡
ምንጭ፡- (“ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች”፤ 2007 ዓ.ም)