አንሶላ እና ‘የዘር ፖለቲካ’

አንሶላ እና ‘የዘር ፖለቲካ’

“ስሙኝማ…እውነት ለመናገር እኮ ብዙ ዘፈኖቻችን እነኚህን አይነት ነገሮች በተመለከተ “ግፋ ወደፊት…” አይነት መልዕክቶች ያላቸው ይመስላሉ… “አሁንስ ከእነ ሚስቱ ሊናፍቀኝ ነው” በሚሉ ስንኞች… “እሽክም እናኑ…” ብለናል፡፡ “እሷ ስትጠፋ እህቷ ተገኘች” በሚሉ ስንኞች “ለእኔም አምጪ፣ ለአንቺም ጠጪ” ስንል አንግተናል፡፡--”
      

    እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ግልጽ ያለ በዛፍና በአረንጓዴ በተሞላ ስፍራ ላይ ሆናችሁ የአየር እጥረት አይሰማችሁም! አንድ ‘የሆነ ሀይል’ ወይም የሆኑ ልተለዩዋቸው ያልቻልችኋቸው ሀይሎች፣ ኦክሲጅን እንዳይደርሳችሁ እያሴሩባችሁ አይመስላችሁም! “ግዴላችሁም ሁሉም ለበጎ ነው” በሚሉት የተስፋ ድምጾች ለመጽናናት እየሞከርንም፣ የምናያቸውና የምንሰማቸው ነገሮች ‘ዘና’ አያሰኙም፡፡
ታዲያላችሁ…እንቅልፍ የሚነሳን አጀንዳ ያጣን ይመስል፣ይሄን ሰሞን ደግሞ ጊዜ የማይሰጥ ‘ሀገራዊ አጄንዳ’ ገጥሞናል፡፡ ባህር ማዶ ያለች አንዲት ተዋናይት፣ ከሆነ ባለትዳር ጋር መርፌ ክር ሆና ተያዘች ተብሎ ይኸው ማህበራዊ ሚዲያው ‘ጧ’ ሊል ጫፍ ደርሶ ከርሟል፡፡ ልክ እኮ እንዲህ አይነት ግላዊ (ፐርሰናል) የሚባል ነገር ሲፈጠር ከምናምን መቶ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነው ያስመሰልነው:: ዝርዝሩን ባናውቀውም (የግለሰቦችን የጓዳ ህይወት የማወቅ መብቱም የለንምና) ምናልባት ‘ቀን የጣላት’ ልትሆን የምትችል ልጅ ላይ ይሄ ሁሉ የእርግማንና የኩነኔ መአት… አለ አይደደል… የምር ያሳዝናል፡፡ እናማ … ስንት አገራዊ ጉዳዮች ከግራና ቀኝ ከበውንም፣  በታሪካችን ምናልባትም በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የህልውና ጥያቄ የሚያስነሱ ነገሮች፣ ከጅረትነት ወደ ጎርፍነት እየተለወጡ በመሰሉበት ሰዓት የግለሰቦች አንሶላ መጋፈፍ እዚህ ያዳርሳል እንዴ!
አለ አይደል… የ‘ድርጊቱ’ ትክክል መሆን አለመሆን ጉዳይ አይደለም… በዓለማዊ ህግጋትም በሐይማኖቶች አስተምህሮዎችም ያሉት አቋሞች ግልጽ ናቸውና!
ግን ደግሞ አሁንም እኮ ይህ ጉዳይ እጅግ ግላዊ ነው፡፡ በቀጥታ የመሚለከታቸው ሦስት ሰዎች፤ እናድርሰው ካላሉ በስተቀር ወደ ችሎት አደባባይም ሆነ ወደ አስታራቂ ሽማግሌዎች ዘንድ የሚደርስም አይደለም እኮ! ነገሩ ምን ያህል ፈር እንደለቀቀ የምታውቁት፣ ሞራላዊነቱና እጅግ ግለሰባዊነቱ ቀርቶ ወደ ዘር ፖለቲካ ጥልቅ ማለቱ ነው፡፡ በጣም የሚዘገንን! ብሎም አስተሳሰባችን በምን አቅጣጫ እየሄደ እንደሆነ ሊያሳስበን፣ ባስ ሲልም ሊያሰጋን የሚገባ ነው፡፡ የኳሱ ነገር እየገረመን… “ጭራሽ ቅሪላም የዘር ፖለቲካ መሳሪያ ሆነችና አረፈችው!” ብለን እንዳልተዘባበትን፣ ‘የዘር ፖለቲካ’ ወደ ግለሰቦች መኝታ ቤት ሲገባ ፖለቲካችን አያሳዝንም!
እናላችሁ…አለ አይደል… ፖለቲካችንም ውስጥ የአስራ አንደኛ ሰዓት ጄንጊስ ካኖች፣ ከየስርቻው ፈልፍለው የወጡ “ታዝዬም ስታገል ነበር፣” ሊሉ ምንም የማይቀራቸው ‘የድል አጥቢያ አርበኞች፣’ ‘የድንኳን ሰባሪ ጀግኖች’--- ለኤክስፖርት በሚያበቃ ደረጃ’ እንደበዙት ሁሉ በእነኚሁ ግለሰቦቹም ጉዳይ ‘የቅዱሳን’ እና ‘የምድራዊ መላእክት’ ቁጥራችን እንደ ‘ኤኮኖሚያችን፣ በሁለት ዲጂት’ ሳይሆን በሁለት ሺህ ሁለት መቶ ዲጂት እየጨመረ ነው፡፡
እሁድ ሰርግ ደግሰው ማክሰኞ ፍቺ መፈጸም በተጀመረባት ሀገር፣ ባል ሳይፈልግ በማስፈራሪያና በተጽእኖ ከሀገር እየተገፋ ሚስት ይነጠቃል በሚባልበት ዘመን፣ ከሌላው ሰው የትዳር ጓደኛ ጋር አንሶላ መጋፈፍ እንደ ‘አድቬንቸር’ በሚቆጠርበት ዘመን፣ ‘መርፌና ክር’ መሆን የእምነትና የሞራል ጉዳይ ሳይሆን እንደ ‘ሪክሬኤሽን’ መታየት በጀመረበት ዘመን፡ ‘መልቲፕል ፓርትነርስ’ (‘ብዙ ወዳጅ’ እንደማለት) መያዝ ከሞራላዊ ድክመትነቱ ይልቅ ‘በሌሎች የመፈለግ’ ምልክት በሆነበት ወቅት፣ ‘ሬጉላር ቦይፍሬንድ’ና ‘ፓርትታይም ቦይፍሬንድ’ የሚባሉ ቋንቋዎች በተፈጠሩበት ዘመን… አለ አይደል… በአንድ ግለሰብ ላይ ይሄ ሁሉ ‘ናዳ’ በምንም መመዘኛ ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡
እናማ…ምን መሰላችሁ፤ እንዲህ አይነት ነገሮች አእምሯችን ምን ያህል ለአሉታዊ ነገሮች እንደሚፈጥን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እዛኛው ሰው ወይም ወገን ላይ የሚታዩን፣ ኪሊማንጀሮን የሚያካክሉ በጎ ነገሮቹ ሳይሆኑ ‘የሰናፍጭ ቅንጣት’ ያህል የማይገዝፉት ጉድለቶቹ ናቸው፡፡ የእኛ ስንትና ስንት ጉድ በየጓዳው፣ በየፔንስዮኑ፣ በየኮንዶሚኒየም የ‘ኢመርጀንሲ’ ቤቱ፣ ከውስጥ በኩል በየሚቆለፈው ቢሮ፣ በየመኪናው የኋላ ወንበር…ስንትና ስንት ጉድ እያለ -- “ከደሙ ንጹህ ነን” ጲላጦስነት ‘ፌይር’ አይደለም፡፡
ካነሳነው አይቀር…በደል ደረሰብኝ ያለችውና የእሷ ወገን ብቻ የተሰማላት ሴት እኮ ማስረጃ የምትለውን ይዛ፣ ሰውየዋን ፍርድ ቤት አቁማ፣ ቤቱንና ሬንጅ ሮቨሯን ጠቅላላ መሄድ ነው፡፡ አራት ነጥብ! ማለት እዚህ ላይ ነው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥፎ ሚሊዮኖች አንዲያዩት ማድረግ ምን አይነት ሞራል ነው?! 
“ስማ የሆነ ማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ደረሰኝ እኮ…”
“ምን የሚል?”
“ከሚስቴ የምትርቅ ካልሆነ፣ ግንባርህን ነው የማፈርሰው የሚል ማስጠንቀቂያ!”
“ታዲያ አንተ ከሰው ሚስት መራቅ ነዋ!”
“እሱ ነው እኮ የቸገረኝ…”
“ግልጽ አይደለም እንዴ! ምኑ ነው የቸገረህ?”
“ስሙን ስላልጻፈ፣ የየትኛዋ ባል እንደሆነ ማወቅ እልቻልኩም”
ስሙኛማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንድ ደጋግመን የምንሰማት ቀልድ ቢጤ አለች:: ልጁ አስተማሪውን “ቲቸር ቆሎ በእንግሊዝኛ ምንድነው?” ይለዋል፡፡ አስተማሪውም ትንሽ አሰብ አደረገና ማጣፊያው ቢያጥረው፣ የ‘ፈረንጅ አፏ’ ነገር… አለ አይደል... ‘ጦጣ ቢያደርገው’ ምን ቢል ጥሩ ነው……
“የታባክ ነው ፈረንጅ ቆሎ ሲበላ ያየኸው!” ብሎ በኩርኩም ቀወረው አሉ፡፡ ዘንድሮ ብዙ ነገሮች በተለይ ‘ቦተሊካው’ ውስጥ ማጣፊያቸው ሲያጥር፣ እናውቃለን ያልነው ነገር፣ ጭራሽኑ ‘ጦጣ’ ሲያደርገን፣ ምላሹ… “የታባክ ነው ፈረንጅ ቆሎ ሲበላ ያየኸው!” አይነት ይሆናሉ፡፡
የምር ግን…ያቺ ልጅ የሆነ ትልቅ በጎ ሥራ ብትሠራ፣ ቤሳ ቤስቲን ሳይቀራት ያለ ንብረቷን ሁሉ ለአንድ ችግረኛ ቤተሰብ በእርዳታ ሰጠች ቢባል፣ አሁን ከምኔው አንድ ሺህኛ ማላሽ እናይ ነበር፡፡ እሷን የምናሞግስ፣ በምድር ላደረገችው በጎ ሥራ በሰማይ ብደሩን እንዲከፍላት የምንመኝላት፣ በወጣ በመቶ እጥፍ ተካ የምንላት ምን ያህላችን እንሆናለን:: አይደለም በየገጻችን ላይ መለጠፍ፣ ከርእሱ አልፈን ታሪኩን የምናነብ አንድ የ‘ኤ ፎር’ ወረቀት እንሞላለን?!
ስሙኛማ.. እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘የወደቀ ዛፍ’ ሲገኝ አቧራ ሲጠጣ የከረመ ዱልዱም መጥረቢያችንን የምንስል ምን ያህል እንደሆንን ከፖለቲካችን የተሻለ ምሳሌ የለም፡፡ ‘መጥረቢያችን’ ምን ያህል ሥራ እንደበዛበት ያለፈው አንድ ዓመት እኮ በቂ ምስክር ነው፤ ስድሳ ስድስትን ተከትለው የመጡት ወራት እኮ በቂ ምስከሮች ናቸው፤ ሰማንያ ሶስትን ተከትለው የመጡት ወራት እኮ በቂ ምስክሮች ናቸው፤ ዘጠና ሰባትን ተከተለው የመጡት ሳምንታት እኮ በቂ ምስከሮች ናቸው:: እና ዛፍ “ወደቀ” ወይ “ሊወድቅ ዘንበል ብሏል” በተባለ ቁጥር ‘ዛፉን’ ብናውቀውም ባናውቀውም፣ በደል ቢያደርስብንም ባያደርስብንም፣ በ‘ዛፉ’ ጉዳይ ቢያገባንም፣ ባያገባንም ‘መጥረቢያ ከመሳል’ ልማድ ካልወጣን የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህች ተዋናይትም የገጠማት ይኸው ነው፡፡ ከግለሰብነቷ ታልፎ ወደ ዘር ማንነቷ የተገባውም በዚህ አይነት አደገኛና አሳሳቢ አስተሳሰብ ጦስ ነው፡፡ 
“አንተ! ምንድነው ጉንጭህ እንዲህ ያበጠው?!»
“ያቺ ባሏ ፊልድ ሄደ ያልኩህ ሴት ትዝ አለችህ?”
“አዎ፣ እና ምን ተፈጠረ?”
“ባሏ ፊልድ አልሄደም፡፡”
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እውነት ለመናገር እኮ ብዙ ዘፈኖቻችን እነኚህን አይነት ነገሮችን በተመለከተ “ግፋ ወደፊት…” አይነት መልእክቶች ያላቸው ይመስላሉ… “አሁንስ ከእነ ሚስቱ ሊናፍቀኝ ነው” በሚሉ ስንኞች… “እሽክም እናኑ…” ብለናል፡፡
“እሷ ስትጠፋ እህቷ ተገኘች” በሚሉ ስንኞች “ለእኔም አምጪ፣ ለአንቺም ጠጪ” ስንል አንግተናል፡፡ “የወንፈሌው ጥጥ ተው አትንቀጥቀጥ” በሚሉ ስንኞች የትከሻ እንቅጥቅጥ እስክስታችንን ስናስነካው ኖረናል፡፡
ኸረ እናውራ ከተባለ ብዙ፣ በጣም ብዙ ነገር አለ! እናማ…የግለሰቦችን የጓዳ ህይወት፣ ሀገራዊ አጄንዳ አስመስሎ፣ ሲብስም በሌሎች የህይወት ዘርፎች መከራችንን እያበላን ያለውን ‘የዘር አጄንዳችንን በግለሰቦች ‘አንሶላ ስር’ መክተት አሪፍ አይደለም፡፡ አንሶላ የዘር ፖለቲካ ‘ኮንስፒሬሲ ቲየሪ’ ዋና ክፍል የሆነባት ሀገር የእኛዋ ጦቢያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!