እሷና እሱ፤ (በአማራጭ) እሱና እሷ

እሷና እሱ፤ (በአማራጭ) እሱና እሷ

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ…
አንድዬ፡— አጅሬው ምነው ጠፋህ? ምነው ጠፋህ ልበል እንጂ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምኑን እጠፋለሁ:: ጠዋት ማታ የአንተን ስም ሳላነሳ ውዬ አድሬ አላውቅም፡፡ አንድዬ… ነጋ ጠባ እንደዛ አንጋጥጬ ስለማመንህ ነገሬ አላልከኝም ማለት ነው!
አንድዬ፡— ነገሬ የምላቸው ጉዳዮች አላጣሁም፡፡ ይልቅ ዛሬ ምን እንዳመጣህ ንገረኝ:: ደግሞ አጠገብህ ያለችው ማነች?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እሷንም አላውቃትም እንዳትለኝ!
አንድዬ፡— አንተ ሰውዬ ምን ነክቶሀል! እያንዳንዳችሁን ማወቅ አለብኝ እንዴ! ይህን ያህል ሥራ የፈታሁ መሰለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡—  አንድዬ አትቆጣ እንጂ!
አንድዬ፡— ጭራሽ አታውቃትም ወይ ትለኛለህ! ስማ…መጀመሪያ እናንተ ራሳችሁን ትውቃላችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዴታ አንድዬ፣ በደንብ እንጂ!
አንድዬ፡— አታውቁም፡፡ ራሳችሁን ያወቃችሁ ይመስላችኋል እንጂ አታውቁም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ኸረ አንድዬ ይሄን ያህል እንኳን አልባሰብንም፡፡
አንድዬ፡— አንቺስ ምን እግር ጣለሽ!
ልጅትዬው፡— አንድዬ፣ መቼም አንተ ፊት በመቅረቤ እንዴት አድርጎ ደስ እንዳለኝ…
አንድዬ፡— ግዴለም፣ እሱን ሌላ ጊዜ ትነገሪኛለሽ:: አሁን ምን እግር እንደጣለሽ ንገሪኝ::
ልጅትዬው፡— አንድዬ ሆድ ባሰኝ! እንዴት ብዬ ላስረዳህ---እንደ ዘንድሮ ክፍት ብሎኝ አያውቅም፡፡
አንድዬ፡— ምን ሆነሽ ከፋሽ!
ልጅትዬው፡— ሰዉ! ሰዉ አንድዬ… ወይ የራሱን ኑሮ አይኖር፣ ወይ ሰው አያስኖር፡፡ አንድዬ፣ እኛ ሴቶች መብታችን አልተከበረልንም:: የወንዶቹን እብሪትና ጥጋብ አልቻልነውም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንቺ! ደግሞ ምን ሆንን ልትይ ነው! ስልጣኑንም፣ ምኑንም ሁሉ ወሰዳችሁ፡፡ ምኑ ቀራችሁ!
ልጅትዬው፡— ምን ቀራችሁ ነው ያልከው! በየቤቱ፣ በየመንገዱ፣ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየመዝናኛው…
ሁሉ ስፍራ አላስቆም፣ አላስቀምጥ ብላችሁን የለ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ታዲያ ይሄንን የማይረባ ነገር ነው አንድዬ ዘንድ ይዘሽ የምትመጪው!
አንድዬ፡— እና ምን ይዛ ትምጣ! እንዳንተ በየጊዜው እየተመላለሰች አልጨቀጨቀችኝ! እርሟን ብትመጣ አንተ ምንህ ተነካ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ምን መሰለህ…
ልጅትዬው፡— ጉዳቸው እንዳይወጣ ነዋ፣ አንድዬ፡፡ አፍ አፌን የሚለኝ ጉዳቸው እንዳይወጣ ነው፡፡ ሂድና የምታሸማቅቀውን አሸማቅ፡፡ አንድዬ ፊትማ እንደ ልቤ ነው የማወራው!
አንድዬ፡— እናንተ ሰዎች አሁን፣ አሁን የባሰባችሁ አመል አሁን ልጅቱ ያለችው ነው:: አንዳችሁ ሌላኛችሁን እያሸማቀቃችሁ እንዴት ብላችሁ ነው የምትደማመጡት!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ከዚህ ችግር እንድንወጣ አንተ አግዘና! በሆነ ተአምር እንድንደማመጥ አድርገን፡፡
አንድዬ፡— የምትገርሙ ሰዎች ናችሁ:: አንዳንድ ጊዜ እኮ ችግራችሁን ሁሉ ያመጣሁባችሁ ነው የምታስመስሉት፡፡ ለእናንተስ ሌላው ያለው አይነት ጆሮ አይደል እንዴ የሰጠኋችሁ! ወይ እናንተ ሞደፊክ የምትሉት ጆሮ አልገጠምኩላችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ ልክ ነህ፡፡
አንድዬ፡— እና…በገዛ እጃችሁ ጥርቅም አድርጋችሁ የደፈናችሁትን እኔ ምን ላድርጋችሁ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ቢሆንም፣ አንድዬ… ቢሆንም ዘዴ አታጣም፡፡
አንድዬ፡— ይኸው፣ እኔ ፊት በትንሹ እንኳን ወገንህ የሆነችውን ማዳመጥ አልፈለግህም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ የእሷ አነጋገር ልክ አይደለማ! እነሱ ስልጣኑን ሁሉ ይዘው ለእኛ እኮ የሚተርፈን ወንበር ሊጠፋ ነው፡፡
አንድዬ፡— ስማ፣ እኔ ዘንድ መጥተህ አላስከፋህም ብዬ ነው እንጂ በዚህ አነጋገርህ ከት ብዬ ብስቅብሀ ደስ ባለኝ፡፡
ልጅትዬው፡— አንድዬ፣ ሁሉም ያው ናቸው፡፡ ሁሉም የሚሳቅባቸው ናቸው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንቺ! አሁን…ብቻ ተዪው:: ቦታችን ስንመለስ እኔና አንቺ እንነጋገራለን፡፡
አንድዬ፡— ለምን እዚሁ አትነጋገሩም! እንደውም እኔ ለትንሽ ደቂቃ ዘወር ልበልላችሁና እዚሁ የፈለጋችሁትን ተነጋገሩ፡፡
(አንድዬ ከአካባቢው ዘወር ይላል፡፡)
ምስኪን ሀበሻ፡— ሴትዮ!!
ልጅትዬው፡— ጎሽ የእኔ አንበሳ! ገና እሱ ዘወር እንዳለ ሴትዮ አልከኝ! ሁላችሁም እኮ እንዲሁ ናችሁ፡፡ የሚታዘብ በሚኖርበት ጊዜ “ስሞትልሽ! ስፈለጥልሽ! ስቆረጥልሽ!” ምናምን ትላላችሁ:: ታዛቢ ሳይኖር ደግሞ… “ድብን በይ! ተፈለጪ! ተቆረጪ!” ትላላችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እና ታዲያ ምንም ቢሆን እዛው እኛው በእኛው እንነጋገራለን አንጂ በአደባባይ መለፍለፍ አለብሽ!
ልጅትዬው፡— ይኸው ናችሁ፡፡ ዘላለማችሁን ይኸው ናችሁ፡፡ ችግራችሁን በአደባባይ አውጥታችሁ ፍርጥርጥ እንደማድረግ “ሰው ምን ይላል!” “አገርስ ምን ይላል!” እያላችሁ…
ምስኪን ሀበሻ፡— በአንቺ ቤት ፖለቲካ መናገርሽ ነው፡፡ ጭራሽ የሞቀ ቆዳ ወንበር ሲሰጣችሁ ልታስተምሩን ፈለጋችሁ!
ልጅትዬው፡— ይቆጭሀል፣ አይደል?
ምስኪን ሀበሻ፡— ምኑ ነው የሚቆጨኝ?
ልጅትዬው፡— ያቺ ሴት አለቃህ “ይህን ስራ በአንድ ሳምንት ውስጥ አጠናቀህ ሪፖርት እንድታደርግልኝ” ስትልህ፤ ወይም ሌላ ትእዛዝ ስታዝህ ይቆጭሀል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— (በቁጣ) እሷ ማነችና ነው እኔን እ…አሁን ስለ አለቃ ማን አወራ! እኔ ያልኩት ለምን ችግራችንን…
ልጅትዬው፡— ጉዳችንን በል እንጂ! ቢያንስ አጠገባችን ታዛቢ ስለሌለ፣ አንድዬም ስለማይሰማን ጉዳችንን በል እንጂ!
ምስኪን ሀበሻ፡— ጉድ በዪው፣ ጉድጓድ በዪው የራስሽ ጉዳይ ነው፡፡ የምን አደባባይ አውጥቶ አገር ይስማልኝ ነው፡፡
ልጅትዬው፡— ይኸው ስንቀብር፣ አፈር ስናለብስ የቆየነው ነገር ሁሉ አደባባይ እየወጣ ዓለም እየሰማው አይደል እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንቺ ሴትዮ!
ልጅትዬው፡— እስቲ ለዛሬ አንኳን ይሄን ‘ሴትዮ’ የሚለውን ተወውና በስሜ ጥራኝ፡፡ እሱም ከከበደህ እህቴ፣ እህቴ ከከበደህ ወይዘሮ፣ ወይዘሪት፣ እማሆይ የ.ፈለግኸውን በለኝ፡፡ ይሄ ‘ሴትዮ’ የምትለውን አስቀያሚ ንግግር እስቲ ተወኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ብቻ ምን ታደርጉ፣ ‘ፍየል ከመድረሷ ቅጠል መበጠሷ’ ነው የሚሉት አይደል…
ልጅትዬው፡— ውይ፣ እሱ እኮ ተለወጠ:: “ሴቷ ከመድረሷ አቅሟን ማሳየቷ” ነው የሚባለው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— እውነት! ብላችሁ፣ ብላችሁ ስንት ዘመን የኖረ ተረታችንን ልትለውጡ ነው!
ልጅትዬው፡— ብንለውጥስ ምን ይለናል! አይደለም ተረት የፈለግነውን ብንለውጥ ምን ይለናል! እንደውም እናንተ ጭንቅላት ውስጥ የተከማቸውን የአስተሳሰብ እምቦጭ አረም ጥርግ አድርገን ነጻ እናወጣችኋለን፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— የፈለግሽውን በይ…አሁን ከአንድዬ ጋር ጉዳያችንን ጨርሰን ወደመጣንበት፡፡
ልጅትዬው፡— ጉዳያችንን ሳይሆን ጉዳዮቻችንን ነው የሚባለው፡፡
(አንድዬ ይመለሳል፡፡)
አንድዬ፡— ስትለፈልፉ እዚሁ ልታድሩ ነው እንዴ! እሺ አሁንስ፣ ብቻችሁን የሆድ የሆዳችሁን ተነጋገራችሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ምን የሆድ፣ የሆድ አለ! ጭራሽ አንጀቴን አቆሰለችው እንጂ!
ልጅትዬው፡— የቆሰለው የማን አንጀት እንደሆነማ አንድዬ ያውቀዋል፡፡
አንድዬ፡— የምትገርሙ ናችሁ! በጣም የምትገርሙ ናችሁ፡፡ ምን እናደርግ መሰላችሁ፣ እናንተ ተደማምጣችሁ በአንድ አፍ መናገር ስትጀምሩ፣ ያኔ እኔም ነገሬ ብዬ አዳምጣችኋለሁ:: በሉ፣ ደህና ሁኑ፡፡
(አንድዬ ዘወር እንዳለ እሱዬው ቡጢ ጨበጠ፣ እሷዬዋ ጥርሷን ነከሰች፡፡)
ደህና ሰንብቱልኝማ!