ከ1 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች በትግራይ ታግተዋል ተባለ

ከ1 ሺህ በላይ የውጭ ዜጎች በትግራይ ታግተዋል ተባለ

አሜሪካ ዜጎቿን ለማውጣት የመንግስትን ፈቃድ እየጠበቀች ነው

             በቅርቡ በትግራይ ድንገት የተጀመረውን የፌደራል መንግስትና የህወሃት ውጊያ ተከትሎ ከ1 ሺ በላይ  የውጭ አገር ዜጎች ከትግራይ ክልል መውጣት አቅቷቸው እንደታገቱ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት አስታውቋል፡፡
ቀደም ሲል በተለያዩ የሠብአዊ ድጋፍ ስራዎች ላይ በክልሉ ተሰማርተው የነበሩ ከ1 ሺህ በላይ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች በግጭቱ ሳቢያ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንዳልተቻለ የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ ነው፡፡
ቀደም ሲል ከሰራተኞቹ ጋር በስልክና ኢንተርኔት ይደረግ የነበረው ግንኙነት በክልሉ ስልክና የኢንተርኔት ግንኙነቶች መቋረጣቸውን ተከትሎ ሁኔታውን አሳሳቢ እንዳደረጉት ዘገባው አመልክቷል፡፡
(ረቡዕ እለት) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር በስልክ የተወያዩት የአሜሪካው የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ቲቦር ናጅ አገራቸው የዜጎቿ ጉዳይ እንደሚያሳስባት አንስተው ዜጎቿን ከክልሉ ለማውጣት የኢትዮጵያን መንግስት ፈቃድ እየተጠባበቁ መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል።
መንግስት በክልሉ ዳግም ሰላም የሚሰፍንበትና ውጥረቶች ሊረግቡ የሚችሉበት እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጠይቀዋል የተባሉት ቲቦር ናጅ፤ አሜሪካ በግጭቱ ለዜጎቿ መስጋቷን ጠቅሰው ለዜጎች አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው፤ አሁን ግጭቱ በሰላም እንዲፈታ፣ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት እንዲከፈትና የሰዎችን ሰብአዊ ደህንነት መከታተል እንዲቻል ጠይቋል፡፡
መንግስት በክልሉ የሚያከናውነው ኦፕሬሽን ህግን የማስከበር በመሆኑ ንጹሃን ዜጎች የጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ ይደርጋል፤ ህግ የማስከበር ተልዕኮውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብሏል፡፡