ሶስቱ ጄኔራሎችና አክቲቪስቶች እየተናበቡ ነው?

ሶስቱ ጄኔራሎችና አክቲቪስቶች እየተናበቡ ነው?

እንዲህ እናድርግ፡- ልማትና እድገት ሶስት ምዕራፎች እንዳሏቸውና ሶስቱም ምዕራፎች የየራሳቸው ጄኔራሎች እንደሚኖራቸው እናስብ፡፡  እንደምታውቁት፣ “ወቅት” “የጎበዝ ያለህ! የመሪ ያለህ! የሰው ያለህ!” ብሎ ሲጣራ “የቁርጥ ቀን ጄኔራሎች” ሆነው ከተፍ፣ ከች የሚሉ ግለሰቦች  ሁሌም አሉ፡፡ “የጊዜን ጥሪ” ከሌሎች ቀድመው ለመስማት ንቁዎች የሆኑ፤ የቆረሱትን ሳይጎርሱ፣ የጎረሱትን ሳያላምጡ፣ ያላመጡትን ሳይውጡ “አቤት!” ለማለት ቅንና ፈጣኖች መቼም ይኖራሉ፡፡ የዚህ አይነት ሰዎች ለመመራት በሚፈልጉ ሰዎች እስኪገፉ አይጠብቁም፡፡ ራሳቸው ናቸው ከመሀከል ተነስተው “ጎበዝ፤ እስቲ መንገድ ልቀቁ! ገለል ገለል በሉ!” ብለው ከፊት ብቅ የሚሉት፡፡  በህይወት ዘመናችን የምናውቃቸው ጀግኖች ብዙዎቹ እንደዚያ ናቸው፡፡
እርግጥ ነው፤ በልመና - መሪ የሚሆኑ ወይም መሪ የሚደረጉም ሰዎች አሉ፡፡ ሰዎቹ በሌሎች ሰዎች የቀረበላቸውን ጥሪ የሚቀበሉት እያመነቱ ሊሆን ቢችልም፤ በራሳቸው ሰዓት በጄኔራልነት እንደሚሰለፉ መሪዎች ሁሉ፤ የመሪነት ሚናቸውን አሳምረው ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ተገፍተውም ሆነ በራሳቸው እጅ መንገድ ከፍተው በመሪነት ከፊት የሚሰለፉት ጄኔራሎች ከባህሪ አንጻር ሲታዩ በአይነት ሶስት ናቸው።
ነፍስ-አድን ጄኔራሎች (emergency generals)፡፡ እነዚህ ጄኔራሎች የሚከሰቱት ህይወት ለህልውና አደጋ በተጋለጠ ጊዜ ነው - በቅድሚያ ነፍስን ለማዳን ሩጫ በሚያስፈልግበት ሰዓት ደቂቃና ሴኮንድ፡፡ ጄኔራሎቹ በባህሪ ፈጣን፣ ደፋር፣ እርምጃ ለመውሰድ የማያመነቱ፣ ራሳቸውን ከጥቃት ለመከላከልም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ከአደጋ ለመታደግ ሲሉ ህይወታቸውንም ቢሆን ለመሰዋት የማይሳሱ የጀብድ ሰዎች ናቸው፤ የጀብድ አዎንታዊ ትርጉም ላይ ይሰመርልኝና፡፡
ነፍስ-አድን ጄኔራሎች የሰከነ ውይይት፣ የአቃቂር፣ የትንተና ወዘተ ሰዎች አይደሉም። ምክንያቱም እነሱ ብቅ የሚሉበት ወቅት ድባብ  እግርን ዘርግቶ፣ አጀንዳ ቀርጾ መወያየት፣ መጽሀፍትን አገላብጦ፣ አዋቂ አማክሮ መላ መላ ማለት ቅንጦት ሆኖ የሚታይበት ነው - የጥድፊያ! የወከባ! የቀውጢ … የነፍስ-ውጪ፣ የነፍስ-ግቢ …  እንዲሉ አይነት፡፡  በደራሽ ወንዝ በመወሰድ ላይ ያለን ህፃን ለመታደግ  በድንገት ከተፍ የሚሉ ዓይነት ሰዎችን ነው ነፍስ-አድን ጄኔራሎች ያልኳቸው፡፡ ጄኔራሎቹ  “አረ ሰው በጎርፍ ወይም በደራሽ ውሀ ተወሰደ …!” የሚል ጥሪ ሲሰሙ “የት … ?!” ከማለት ያለፈ ጥያቄ የላቸውም፡፡  ፈጣን ምላሽ ሲጪዎች ናቸውና ሲሻቸው ከነልብሳቸው፣ አሊያም ከላይ የለበሱትን ጋቢ ብቻ  አሽቀንጥረው እመር ብለው ወንዝ ውስጥ ይገባሉ፤ ብቅ ጥልቅ ብለው ዋኝተውም ለሞት ራት ሊሆን የነበረን ህፃን እንደ አሳ አንጠልጥለው ያወጡታል፡፡
ከዚያስ? ከዚያማ አበቃ፡፡ ጄኔራሎቹ የራሰ ልብሳቸውን አወላልቀው፣ ጨማምቀው - ከፊል እርጥብ ከፊል ደረቅ እንደለበሱ ወደ ቀጣይ ተግባራቸው ይዘልቃሉ፡፡  የሚያደንቅ ያደንቃቸዋል፣ የሚመርቅ ይመርቃቸዋል፣ የሚያመሰግን ያመሰግናቸዋል፡፡ እነሱ ግን ማን ምን እንዳላቸው ለመስማትም የሚፈልጉ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ቀሪው ታሪክ ነው፡፡ ቀጣዩ ተግባር የምዕራፍ ሁለት ጄኔራሎች ይሆናል፡፡
እግረ መንገድ ጠቅሶ ለማለፍ ያህል፡- ነፍስ አድን ጄኔራሎችን ወደ ድርጊት የሚጋብዙት የምዕራፉ አንድ አክቲቪስቶች (ነቅተው አነቃቂ) ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ናቸው - ነፍስ አድን አክቲቪስቶች እንበላቸው፡፡ አጯጯሁን፣ ጀግና አጠራሩን ያውቁበታል። ተርበትብተው፣ ሁለት ሌባ ጣታቸውን ሁለት ጆሮአቸው ውስጥ ዶለው “አረ ሰው  በ … ጎ … ርፍ ተ … ወ … ሰደ!”እያሉ አንዴ ዛፍ ላይ ወጥተው አንዴ ጉብታ ላይ ቆመው ለመጣራት የሚቀድማቸው የለም። “ሰው በጎርፍ እየተወሰደ እንዴት ዝም ይባላል?” እያሉ በዙሪያቸው ያለውን ሰው ይቀሰቅሳሉ፡፡ ያኔ ነው አንዱ ጥሪያቸውን ቀድሞ የሰማ ጄኔራል ከተፍ የሚለው። የዚህ ምዕራፍ አክቲቪስቶች ሚና ከዚህ አያልፍም፡፡  ልክ እንደ ጄኔራሎቹ ሁሉ ከነፍስ አድን አክቲቪስቶች ተጨማሪ ሚና መጠበቅ ስህተት ነው፡፡ ቀጣዩ ተግባር ተጨማሪ እውቀትና ዝንባሌ ያላቸው የምዕራፍ ሁለት አክቲቪስቶች ነው፡፡  
ምዕራፍ 2. እፎይታ ሰጪ/የመልሶ ማቋቋም ጄኔራሎች (rehabilitation generals)፡፡ እነዚህኛዎቹ  ህይወት ከተረፈ በኋላ የሚከሰቱ ናቸው፡፡  ቅድም ያየነው ከውሀ ውስጥ የወጣው ህፃን የጠጣው ውሀ ከሆዱ እንዲወጣ፣  ተጨማሪ የህክምና እርዳታ እንዲያገኝ … እንዲበላ፣ እንዲጠጣ፣ …. ወዘተ ሁኔታዎችን በፍጥነት የሚያመቻቹ እነዚህ ጄኔራሎች ናቸው፡፡ ተፈላጊው ድጋፍ በወቅቱ እንዲደርስ ነገሮችን ማሳለጥ ይችሉበታል፡፡  በባህሪ ደግ፣ ርህሩህ፣ ርብትብት ናቸው፡፡ አነዚህኛዎቹ ጄኔራሎችም ልክ እንደ ምዕራፍ አንድ ጄኔራሎች የስብሰባ፣ የረዥም ወይይት ሰዎች ያልሆኑ ነገር ግን ነገሮችን በፍጥነት የሚያስኬዱ ናቸው፡፡ ተግባራቸውም ከጎርፍ የተረፈ ህፃን ጤናው እንዲያገግም እስከመርዳት ድረስ ብቻ ይሆናል፡፡ ቀጣዩ ተግባር የሌላ ጄኔራል ነው፡፡  
ይህም ምዕራፍ የራሱ አክቲቪስቶች አሉት፡፡ አክቲቪስቶቹ ምዕራፉ ሊያካትታቸው የሚገባ ተግባራትን ቀደም፣ ቀደም በማለት እየጠቃቀሱ በተጎዳው ህፃን ስም “ለሚመለከታቸው” አካላት አቤቱታ ያሰማሉ፡፡ ለምሳሌ፤ የህፃኑ ትምርት … ቤተሰቦቹን የማፈላለግና የማገናኘት ጉዳይስ…? በማለት ተረጂው ተጨማሪ ድጋፎች እንዲደረጉለት ይጎተጉታሉ፡፡
እዚህ ላይ ታዲያ፣ ልክ ቀደም ሲል እንዳነሳናቸው አክቲቪስቶች ሁሉ፤ እነዚህኛዎቹም አክቲቪስቶች የአውቀት ወይም የሚና ውስንነት አላቸው፡፡ ለምሳሌ፤ ስለዘላቂ ልማት አያነሱም፡፡ ከእነሱ ይህን መጠበቅ ስህተት ነው፡፡
ምዕራፍ 3. የዘላቂ ልማት ጀግኖች (development generals):: እነዚህኛዎቹ ጄኔራሎች ብቅ የሚሉት በጎርፍ ሊወሰድ ይችል የነበረ ህፃን ከሞት ከተረፈና ህይወቱን ለማቆየት የሚያስችሉ ተግባራት ከተከናወኑ በኋላ ነው፡፡  ለስብሰባ፣ ለውይይት፣ ለጥናት በቂ ጊዜ ይመድባሉ፡፡ ሩቅ አሳቢ እንደመሆናቸው፣ ህፃኑ መደበኛ ህይወቱን በዘላቂነት እንዲቀጥል የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት አልፈው “ለወደፊትስ ተመሳሳይ የውሀ ሙላት ችግር ህፃናትን እና ሌሎች አቅመ ደካሞችን እንዳይጎዳ ምን አይነት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅ…?” እያሉ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከልማት ጄኔራሎች በጎርፍ በመወሰድ ላይ የሚገኝን ህፃን በዋና የማውጣት ፈጣን ምላሽ መጠበቅ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ዋነተኛነት፣ ጀብደኝነት ዝንባሌያቸውም ክህሎታቸውም አይደለም፡፡ እነሱ፣ ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ ከስሜታዊነት ውጪ፣ ስክን ብለው ነገሮችን መመልከት የሚመቻቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱን፤ ያልሆኑትን እንዲሆኑ የጠበቅን ቀን እናዝናለን፡፡ እነሱንም እናሳዝናለን፡፡ የዚህ ምዕራፍ አክቲቪስቶች ከቀዳሚዎቹ መሰሎቻቸው በቁጥር የሚያነሱ፣ አስተያየታቸው ከስሜት ይልቅ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ናቸው፡፡ ከላይ እንደተመላከተው ሁሉ፤ የምዕራፍ ሶስት አክቲቪስቶች የምዕራፍ አንድ አክቲቪስቶችን ሚና እንዲጫወቱ ቢጠየቁ “ትንፍሽ” ላይሉ ይችላሉ፡፡
እዚህ ላይ፡- በሶስቱ ምዕራፎች መካካል የማይደረመስ አጥር ያለ ያስመሰልኩት ለትንተና እና ለግብዛቤ ያህል ነው፡፡ ዋናው መልዕክቴ እያንዳንዱ ምዕራፍ የራሱ ጄኔራል አለው፤ ከእያንዳንዱ ጄኔራል መጠበቅ ያለበትም ያ ጄኔራል ምላሽ ለመስጠት ከተሰለፈበት ዓላማ አንፃር ብቻ ነው - የሚል ነው፡፡ ሰዎች፣ የነፍስ-አድን ጄኔራሎችን በፉጨትና በጭብጨባ ብዛት “የመልሶ ማቋቋምም ጄኔራሎቻችን ሁኑልን! … የልማት ጄኔራሎቻችንም በቃ እናንተው ሁኑልን!” ይሉ ይሆናል፡፡ ወይም በግልባጩ፤  ጄኔራሎቹ ቢያንስ የሁለት ምዕራፎችን ሀላፊነቶች ለመሸከም ይደፍሩ ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ ምዕራፍ የተለየ ባህሪ ያለው በመሆኑ የጄኔራሎቹ ድካም የበዛ መሆኑ ግን አይቀርም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም። ጄኔራሎቹ ከምዕራፍ ወደ ምዕራፍ በተሸጋገሩ ቁጥር በቀደመ ምዕራፍ ላይ የተመዘገበላቸውን ነጥብ ሊጥሉ ይችላሉ።  እርግጥ ነው - ለጄኔራሎች ያለመተካካት የራሱ የሆኑ ተጨባጭ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ወደ አክቲቪስቶች ስንመጣ፡- የምዕራፍ አንድ አክቲቪስቶች በጭብጨባና ፉጨት ብዛት፣ የምዕራፍ ሁለትም፣ የምዕራፍ ሶሰትም አክቲቪስቶች እንዲሆኑ በሰው ሊጠየቁ ወይም እነሱ ራሳቸው የሁሉም ምዕራፍ አክቲቪስት ሆነው ለመቀጠል ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ይሞክሩ፡፡ ነገር ግን ውጤታማነታቸው መቀነሱ፣ የሚደርስባቸው ሸክምም መብዛቱ አይቀርም፡፡ ምዕራፉን የማይመጥን አክቲቪዝም ገንቢ ሳይሆን አፍራሽ ሊሆንም ይችላል፡፡ ይህንንም ነው ማሰብ፡፡  
ወጌን ለማለዘብ ያህል አክቲቪስቶች ላይ ሊሰራ ይችላል ብዬ ያሰብኩትን ሌላ ነገር ላጋራችሁማ፡፡ መደምደሚያዬ ከታች ይጠብቃችኋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ከጓደኞቻቸው ጋር ወደ ምሽት ቤት በ”እስቲ ልየው” ስሜት ይገቡና፣ ጥግ ይዘው መጠጥ እየተጎነጩ ሳለ ከጓደኞቻቸው አንዱ ብቻውን ሲደንስ ቆይቶ፣ “ተነስ እንጂ እንደነስ!” ይላቸዋል። ይኄኔ፣ የጨበጣቸውን እጅ በቁጣ መንጭቀው “እምቢ፣ አልነሳም” ይላሉ፡፡ ትንሽ ቆይተው ግን ጫናው፣ ጉተታው ሲበዛባቸው ተመዘው፣ ተነስተው እግራቸውን ወርወር፣ ወገባቸውን ሰበቅ፣ እጆቻቸውን ብድግ መለስ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡  ከዚያስ? ከዚያማ አበቃ፤ ወደ መቀመጫቸው ተመልሰው የደናሽ ተመልካች አይሆኑም፡፡ እንኳንስ ሊቀመጡ ቁጭ ብሎ የሚመለከት ታዛቢም ይደብራቸዋል፡፡ “ዳንስ ቤት መጥቶ ያለመደነስ፣ ተደብሮ መደበር፤ ምን የሚሉት ሞኝነት ነው?” ብለው እስከ መገረምም ይደርሳሉ፡፡ አንዱ ዘፈን አልቆ ቀጣዩ እስኪጀምር በቆሙበት ይጠባበቃሉ፡፡ የቀጣዩ ሙዚቃ መግቢያ አለሳልሶ የሚጀምር ቢሆን እንኳ እነሱ በአንዴ ከፍተኛ መረግረግ ላይ ይደርሳሉ። በተለይ ሞቅታ የጀማመራቸው ከሆነማ ተውት፤ የማያዉቁትንም ሰው ሳይቀር “ወንድሜ ተነስ እንጂ ደንስ…! ፈታ በል!” ብሎ መጎተት ይዳዳቸዋል፡፡ እና፤ ምን ለማለት ነው? ልክ ለዳንስ ተጎትጉቶ እንደተነሳና - የመጀመሪያው ዘፈን ካለቀ በኋላ የቀጣዩን ዘፈን ድምድምታ ቆሞ በናፍቆት እንደሚጠብቅ፣ ሙዚቃው ፈጣን ይሁን ለስላሳ ሳይሆን ገና በመግቢያው ሙዚቃ ድምጽ እንደሚረገረግ ደናሽ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖሊቲካዊ ኩነቶችን (በቂ መረጃ ሳይኖቸው) ለማናፈስ አሰፍስፈው የሚጠብቁ አክቲቪስቶች አሉ። ጥያቄ አለኝ፡፡ አሁን አገራችን ያለችው የትኛው ምዕራፍ ላይ ነው፤  የነፍስ አድን፣ የእፎይታ ሰጪ (የመልሶ ማቋቋም) ወይስ የዘላቂ ልማት ምዕራፍ ላይ? አክቲቪስቶች፤ ይህን ሳታጣሩ ጩኸት ለማሰማት ዛፍ ላይ አትውጡ ወይም ጉብታ ላይ አትቁሙ።  ነጥብ ለመጣል አትቸኩሉ!  ጄኔራሎችና አክቲቪስቶች ተደማመጡ፣ ተናበቡሉን እባካችሁ፡፡