እንዴት ሰው እንጣ?

እንዴት ሰው እንጣ?

‹‹ሰማይ ተቀደደ ቢለው፣ ተወው ሽማግሌ ይሰፋዋል›› አለ
                   
            አፄ ቴዎድሮስ የጭካኔ ቅጣት የጀመሩት ወደ ሥልጣን ገና ሳይመጡ ነው፡፡ ከዱኝ ያሏቸውን ሽፍታ ጓደኞቻቻውን እግራቸውን እየጎመዱ ነው ያሰናበቷቸው፡፡ ደረስጌ ማርያም ላይ ዘውድ ጭነው ከነገሡ በኋላ አዋጅ አስነገሩ። አዋጁ አባት ያለህ በአባትህ ሥርዓት እደር፣ አባት የሌለህ አባትህ እኔ ነኝ፤ ደጅ ጥና  የሚል ነበር፡፡
ቴቤዝ በሚባል አካባቢ በዝርፊያና በስርቆት የሚተዳደሩ ሶዎች ነበሩ፡፡ ንጉሡ በአባት ወጉ እደር ሰላሉ ይህን ለማስፈቀድ ወደ ንጉሡ ተወከለው ሰዎች ይመጣሉ፡፡ ለንጉሡም ከአባት ሲወርድ የመጣላቸው መስረቅ መዝረፍ መሆኑን ገልጠው፤ ንጉሡ እንዲያጸድቁላቸው ጠየቁ፡፡
‹‹አናንተ ብቻ ናችሁ ወይስ ሌሎችም ሰዎች አሉ?›› አሉና ጠየቋቸው፡፡
‹‹ብዙ ወንድሞቻችን አሉ፤ እኛ በእነሱ ተልከን ወደ ንጉሡ የቀረብን ነው›› ሲሉ መለሱ። ንጉሡም ወደ መንደራቸው ተመልሰው አንድም ሳያስቀሩ ወገኖቻቸውን ይዘው እንዲመጡ አዘዙ፡፡ በትእዛዙ መሠረት፤ሰዎቹ በተሰበሰቡ ጊዜ ቴዎድሮስ ያልተጠበቀ ውሳኔ ወሰኑባቸው። ሁሉም አንድ አጃቸውንና አንድ እግራቸውን እንዲረጡ አዝዘው አስቆረጧቸው፡፡
አንድ ቀን በሰፈር ሲዘዋወሩ ቴዎድሮስ ላይዋ ላይ ምንም ልብስ ያለበሰች ሴት ያገኛሉ። የለበሱትን ሸማ ከትክሻቸው አንስተው ያለብሷታል፡፡ ከወልዳሚር አምሰት ብር ተበድረው ይሰጧታል፡፡ ላበዳሪያቸው መቶ ብር አድርገው ይመልሱለታል፡፡
ባለቤታቸው እትጌ ምንትዋብና አማካሪያቸው ጆን ቤል ከሞቱ በኋላ አፄ ቴዎድሮስ በቀላሉ የሚበሳጩና ከፍተኛ ቅጣት የሚቀጡ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ደራሲው ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት፤ ይህኛውን ቴዎድሮስ አያውቁትም ባይባልም፣ ልባቸው ውስጥ የሚገባ አልሆነም፡፡ የአሳቸው ቴዎድሮስ ጨካኙ ሳይሆን ዘመነ መሣፍንትን የሰበረው  ቴዎድሮስ ነው፡፡  የግርማቸው ቴዎድሮስ "ለምን ተደፍሬ፣ ለምን ተንቄ" የሚለው ኮስታራው  ቴዎድሮሰ ነው፡፡ ሕዝቡንና አገሩን ማሰልጠን የሚፈልገው ቴዎድሮስ ነው የግርማቸው ቴዎድሮስ፡፡ ስለዚህም ጨካኙንና ግፈኛውን ሳይሆን አገር አንድ ያደረገውን ቴዎድሮስን መልሰው በብዕራቸው ‹‹ቴዎድሮስ›› በተባለው ታሪካዊ ተውኔት ፈጠሩት፡፡ ፀጋዬ ገብረ መደኅን  ‹‹ከሞከርኩት ይልቅ ያልሞከሩት ይቆጨኛል›› የሚለውን ቴዎድሮስን አመጣው፡፡ ደራሲያኑ ብርሃኑ ዘሪሁንና አቤ ጉበኛም ስለ ቴዎድሮስ ጽፈዋል፡፡ የብርሃኑ ቴዎድሮስ በሴራ ካሰበው መድረስ አልቻለም፡፡
ሁሉም የጻፉት ሰለ ጨካኙ ቴዎድሮስ አይደለም፡፡ ብዙ ሰዐሊያን አነሱ በተረዱትና በወደዱት መንገድ ቴዎድሮስን ስለዋቸዋል። አንዳቸውም ቴዎድሮስን በክፉ መልኩ አላቀረቧቸውም፡፡ በከፉ ዓይን አላዩአቸውም፡፡ የግርማቸው ተክለ ሐዋርያትን ነፍስ ይማርና፤ ገናናው አጼ ቴዎድሮስ እንደገነኑ እንዲኖሩ አድርገዋል፡፡
አፄ ምኒልክ ሸዋ ላይ የነበራቸውን ሥልጣን ማስፋፋት የጀመሩት፣ ገና ንጉሱ ሸዋ እያሉ፣ በአፄ ዮሐንስ ሥልጣነ መንግሥት ስር ሆነው ነው፡፡ ከነገሡ በኋላም ቀጥለውበታል፡፡ በሰላም የገባላቸውን እየተቀበሉ፣ አልገብርም ያለውን በኃይል እየተዋጉ፣ ካስገበሩ በኋላ መልስው ሥልጣኑ ላይ እያደላደሉ ግዛታቸውን አሰፉ። ከቴዎድሮስ በኋላ ያለችዋን  ኢትዮጵያን ፈጠሩ። ልጅ ኢያሱ በኋላም ራስ ተፈሪ መኮንን የተረከቡት ይህችን አፄ ምኒልክ ያቆሟትን ኢትዮጵያ ነው፡፡ ሆኖም ትልቅ አገር ያስረከቡት አፄ ምኒልክ፣ ሲረገሙ እንጂ  ሲወደሱ አይታይም፡፡ እሳቸው ያስረከቡትን ትልቅ አገር፣ ወደ እድገት ጎዳና ለመውሰድ ከመትጋት ይልቅ የተመረጠው ጎራ ለይቶ፣ የተበዳይነት ትርክት እየፈጠሩ፣ እርስበርስ መወነጃጀል ነው፡፡
ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት በማደራጀት፣ በምስራቅ አፍሪካ የታወቀ የአየር፣ የምድርና የባሕር ኃይል በማቋቋም ስም የሚያስጠራ ተግባር አከናውነዋል፡፡ በአፍሪካ የነጻነት ትግል የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሠረትና ዋና ጽሕፈት ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን በማድረግ፣ አገራችን በአህጉር አቀፍ ድርጅት የላቀ ሥፍራ እንዲኖራት አስችለዋል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ቢሮ አዲስ አበባ መሆኑ አያስገኘ ያለውን የውጭ ምንዛሪ አለማሰብ የዋህነት ነው፡፡
የንገሡን ከአገር መውጣት፣ እንደ መክዳት የሚቆጥሩ ቢኖሩም፣ በአገር ውስጥ አለመኖራቸው የጦርነቱን ማዕከል በመበተን ጠላት የሚይዘው እንዲያጣ ማድረጉን መካድ አይቻልም፡፡  የንጉሡን  ስህተት በማጉላት፣ በጎ ሥራቸው እንዲደበቅ በማድረግ፣ የሚገባቸውን ክርና ሞገስ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ አፄ ምኒልክም ሆኑ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የግርማቸው ተክለ ሐዋርያት አይነት ጸሃፊ ባለማግኘታቸው፣ በጎ ታሪካቸው ለትውልድ በቅጡ አልተላለፈም፡፡
ምኒልክ ሰሜን ጎንደርን ከአፄ ዮሐንስ ለመንጠቅ ተነሱ፡፡ በዚህ የተበሳጩት አፄ ዮሐንስ ጦር ጭነው ሸዋ ገቡ፡፡ ሁኔታው ያላማራቸው የአጽቢ ሐደራ መነኮሳት ‹‹በናንተ ምክንያት የክርስቲያን ደም አይፍሰስ። ታረቁልን›› ብለው ሁለቱን ጉልበተኞች ለማስታረቅ ተነሱ። ጊዜ ቢወስድም እርቁ ሰምሮ፣ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት፣ ምኒልክ ደግሞ ንጉሠ ሸዋ በመሆን ከአስር ዓመታት በላይ አገር መርተዋል፡፡
‹‹ሰማይ ተቀደደ ቢለው ተወው ሽማግሌ ይሰፋዋል›› አለ፤ ይባላል፡፡ ዛሬ በዘመናችን ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ለሽምግልና ወደ መቀሌ ያቀናው የሽማግሌዎች ቡድን፣ የችግሩን እድሜ ከማራዘም ውጪ ያመጣው ውጤት የለም፡፡
እንዴት አንድ እንኳ የሚሰማ ሰው አጣን? እንዴት አንድ እንኳን የሚከበርና የሚታመን ሽማግሌ አጣን? ለሁሉም ነገር ተጠያቂው እኛው ነን፡፡ ሁሉንም ያጠፋነው እኛው ነን። የሽምግልና ባህሉን፣ አገር በቀል የእርቅ ባህልና ወጉን፣ እርስ በርስ የመከባበርና የመደማመጥ ቱባ እሴቱን--ሁሉንም አፈራርሰን የተቀመጥነው እኛው ነን። ውጤቱም ችግሮችን በውይይትና በንግግር ከመፍታት ይልቅ ሳንወድ ተገደን ወደ ጦርነት መግባት ሆነ፡፡  
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይጠብቅ!!!